Skip to main content
news003

በብዝሀ ህይወት ጥበቃና እንክብካቤ ላይ በልዩ ትኩረት በመስራት ሀገር በቀል ዝርያዎችን ማስፋፋት እንደሚገባ ተመላከተ (ዱራሜ ፣ግንቦት 29/2018) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሀዲያ ዞን በሌሞ ወረዳ የጀዌ ነባር ዘር ጥበቃና ልማት ማህበር የስራ እንቅስቃሴ የመስክ ምልከታ ተካሂዷል የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ደንና አካባቢ ጥበቃ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ አብርሐም መጫ እንደገለጹት በክልሉ ነባር ዘር ጠባቂ ማህበራትን ከማደራጀት፣ከማስፋት እና ከማብቃት አንጻር በሁሉም ዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች ዘርፈ ብዙ ስራ ተግባራዊ እየተደረገ ነው ብለዋል። 

ባለፉት ሶስት ዓመታት በሀገር አቀፍ ደረጃ ተሞክሮ ሊቀመርባቸው የሚችሉ 8 ነባር ዘር ጠባቂ ማህበራት ስለመኖራቸው አቶ አብርሐም ጠቁመዋል። ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ መገንባተት የቢሮው አብይ አላማ ነው ያሉት ኃላፊው በዚህም የደን ልማት ስራ ተጠቃሽ መሆኑን አብራርተዋል። በክልሉ ነባር የዘር ባንኮችን በማቋቋም የደን ዝርያን ፣የምግብ ሰብሎችን፣የቅመማ ቅመም እንዲሁም እንስሳትን ጠብቆ የማቆየት ስራ ልዩ ትኩረት እንደተሰጠውም ኃላፊው ተናግረዋል። በቀጣይም የዱር እንስሳት ዝርያዎችን የማንበር ስራ ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቃል ሲሉም ኃላፊው አስረድተዋል። ብዝሀ ህይወት ሚዛኑን ጠብቆ ሲቆይ ለሁሉም ፍጥረታት ተስማሚ ምህዳር መፍጠር ተገቢ ስለመሆኑም አመላክተዋል። የአየር ንብረትን መቋቋም የሚችሉ ሀገር በቀል የሰብል እና የእንስሳት ዝርያዎችን በምርምር የማሻሻል ስራ ተግባራዊ እየተደረገ ስለመሆኑም ኃላፊው ጠቅሰዋል። በኢትዮጵያ ብዙሃ-ህይወት ኢንስቲትዩት የአዝዕርትና ሆርቲካልቸር ምርምር መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ውብሸት ተሾመ እንደገለጹት የሀገሪቱን የብዝሀ ህይወት ሀብት የማቆየት እና ለጥቅም የማመቻቸት ስራ እየተከናወነ ነው ብለዋል። 

በክልሎች የማህበራዊ ዘር ባንክ በማስፋፋት ለብዝሀ ህይወት ጥበቃና እንክብካቤ ልዩ ትኩረት መሰጠቱን ጠቁመዋል። የነባር ዝርያዎችን መመናመን ለማስቀረት በብሔራዊ የዘር ባንክ በማቀዝቀዣ ማቆየት ስለመቻሉም መሪ ስራ አስፈጻሚው አብራርተዋል። ነባር ዝርያዎችን በጥናት በመለየት ምርታማነትን ማሳደግ የሚያስችሉ ስራዎችን ተግባራዊ እየተደረገ ነው ሲሉም ጠቁመዋል። የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ደንና አካባቢ ጥበቃ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አድማሱ ወ/ማሪያም እንደገለጹት በክልሉ በየ አመቱ የደን ሽፋን በ 0 ነጥብ 7 በመቶ እያደገ ነው ብለዋል። እንደ ምክትል ኃላፊው ገለጻ በየአመቱ በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ፕሮግራም የክልሉ የደን ሽፋን 18 ነጥብ 7 በመቶ እድገት አሳይቷል። 

እየተመናመኑ ያሉ የብዝሀ ህይወት ሀብቶችን የመጠበቅ፣የመንከባከብ እና ጠብቆ የማቆየት ስራ ልዩ ትኩረት እንደተሰጠውም አቶ አድማሱ አብራርተዋል። በመርሐ ግብሩ ከፌደራል፣ ከክልል፣ ከዞኖች እና ከልዩ ወረዳዎች የተውጣጡ የስራ ኃላፊዎች፣ ተመራማሪዎች እና አርሶ አደሮች ተገኝተዋል።

Add new comment

Restricted HTML

  • Allowed HTML tags: <a href hreflang> <em> <strong> <cite> <blockquote cite> <code> <ul type> <ol start type> <li> <dl> <dt> <dd> <h2 id> <h3 id> <h4 id> <h5 id> <h6 id>
  • Lines and paragraphs break automatically.
  • Web page addresses and email addresses turn into links automatically.