Skip to main content
news004

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የማኅበረሰብ ዘር ባንኮች ፎረም ምሥረታ የምክክር መድረክ ተካሄደ (ዱራሜ፣ ግንቦት 29/2018 ) የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ደንና አካባቢ ጥበቃ ልማት ቢሮ ዓለም አቀፍ የብዝኃ ሕይወት ቀንን ምክንያት በማድረግ፣ ከ"ፔለም ኢትዮጵያ" ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የማኅበረሰብ ዘር ባንኮች ፎረም ምሥረታና የምክክር መድረክ ተካሂዷል። የቢሮው ኃላፊ አቶ አብርሃም መጫ በመድረኩ ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር፤ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመከላከልና ለመቋቋም የማኅበረሰብ ዘር ባንኮች ያላቸው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል። የዘር ባንክ ከአካባቢ ጥበቃና ከአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ባሻገር፣ ለሥነ-ምግብ ዋስትና እና ለኢኮኖሚ ዕድገት የሚሰጠው ጥቅም ተጠቃሽ መሆኑን አንስተዋል። 

ይህ የዘር ባንክና የአረንጓዴ አሻራ ትስስር ዓላማ ተኮር መሆን እንዳለበት የጠቆሙት ኃላፊው፤ "የትኛውን ተክል የት እንትከል? የትኛውንስ ዘር የት እንጠቀም?" የሚለው በምርምርና በቁርጠኝነት ሊመራ እንደሚገባ አሳስበዋል። በዚህም መሠረት በክልሉ ለሀገር በቀል ዝርያዎች ልዩ ትኩረት መሰጠቱን ጠቅሰው፤ በተለይም በሀበሻ ጎመን፣ በሀገር በቀል ዶሮና ከብት እንዲሁም በሀበሻ ጽድ ዝርያዎች ጥበቃና ልማት ላይ በልዩ ትኩረት እየተሠራ መሆኑን አስረድተዋል። አቶ አብርሃም አክለውም፣ በዚህ ታላቅ ዓላማ ስኬት ላይ የአርሶ አደሮችና የገጠር ልማት ባለሙያዎች ሚና የጎላ በመሆኑ በቀጣይ ሥራዎች ላይ ተባባሪነታቸውን እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል። 

የሆሳዕና ከተማ ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሽጉጤ በበኩላቸው፤ የዘር ባንኮችን ማስፋፋት ከተማዋን ውብና ለሕይወት ምቹ ከማድረግ ባለፈ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እንደሚረዳ ገልጸዋል። ከተማ አስተዳደሩ በቀጣይ የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክቶችን ለመተግበር ባቀደው መሠረት፣ አጋር ድርጅቶች ከጎናቸው እንዲቆሙም ጥሪ አቅርበዋል። በዕለቱ ክልላዊ የማኅበረሰብ ዘር ባንኮች የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት የቀረበ ሲሆን፤ ከዚህም በተጨማሪ የዘር ባንክ ምንነት፣ ጥቅም እና የፎረሙን አስፈላጊነት የሚያብራራ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሰነድ ለተጋባዥ እንግዶችና ለአርሶ አደሮች ቀርቦ ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል። 

በመጨረሻም የመድረኩ ተሳታፊዎች በዘር ባንክ አጠቃቀምና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ያነሷቸውን ጥያቄዎች መነሻ በማድረግ፣ በዘርፉ የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ማብራሪያና ምላሽ ተሰጥቶበት የምክክር መድረኩ ተጠናቋል።

Add new comment

Restricted HTML

  • Allowed HTML tags: <a href hreflang> <em> <strong> <cite> <blockquote cite> <code> <ul type> <ol start type> <li> <dl> <dt> <dd> <h2 id> <h3 id> <h4 id> <h5 id> <h6 id>
  • Lines and paragraphs break automatically.
  • Web page addresses and email addresses turn into links automatically.