Skip to main content
007

በክልሉ ባለፉት ዓመታት የተተከሉ ችግኞች የአካባቢን ስነ ምህዳር በማሻሻል ረገድ ጉልህ ፋይዳ እንደነበራቸው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ደንና አካባቢ ጥበቃ ልማት ቢሮ አስታወቀ። (ሆሳዕና፣ሰኔ 18/2018) በክልሉ በተያዘው በጀት ዓመት በአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራም 124 ሺ ሄ/ር መሬት የሚሸፍን የችግኝ ተከላ እንደሚካሔድም ተመላክቷል የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ደንና አካባቢ ጥበቃ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ አብርሐም መጫ እንደገለጹት የአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራም ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት እያደረገችው ላለው ጥረት ሁነኛ መፍትሄ ነው ብለዋል። በክልሉ ባለፉት ዓመታት የተተከሉ ችግኞች የአካባቢን ስነ ምህዳር በማሻሻል ረገድ ጉልህ ፋይዳ እንደነበራቸውም ኃላፊው አብራርተዋል። 

አለምን እየፈተነ ያለውን የአየር ንብረት ለውጥ ለመቋቋም የአካባቢ ጥበቃና እንክብካቤ ስራ ልዩ ትኩረት ያሻል ብለዋል። በክልሉ ለተከታታይ ዓመታት በተካሔደ የአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራም ምርትና ምርታማነት እያደገ ነው ያሉት ኃላፊው የስራ እድል ፈጠራ፣የከርሰ ምድር እና የገጸ ምድር የውሃ አካላት መጨመራቸውን ጠቁመዋል። 

በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራም በ124 ሺ ሄ/ር መሬት ላይ 530 ሚሊየን ችግኞች እንደሚተከሉ አቶ አብርሐም ጠቁመዋል። በክልሉ ከሚተከሉት ችግኞች 60 በመቶ የሚሆነው የግብርና ልማትን የሚያግዙ መሆኑን የተናገሩት ኃላፊው ቀሪው 40 በመቶ የሚሆነው ደግሞ ለአካባቢ ጥበቃ እና ለኢንዱስትሪ ግብአት የሚውል ነው ። 

በክልሉ እስከ አሁን ከተተከሉ ችግኞች ውስጥ 83 በመቶ መጽደቃቸውን ኃላፊው አስረድተዋል።